የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በያኔው አጠራር መብራት ኃይል የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ተብሎ ይጠራ የነበረው ውድድር ወደ ሊግ ተቀይሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚል ስያሜ በስምንት ክለቦች መካከል እንደ ኢትዮጵያውያኑ አቆጣጠር በ1990 መካሔድ ሲጀምር የመጀመሪያውን ዋንጫ በማንሳት ከአገሪቱ ክለቦች ቀዳሚ ነው፡፡ሊጉ በቀጣዩ ዓመት ተሳታፊዎቹን ወደ አስር በማሳደግ ሲቀጥል ደግሞ የአስራት ኃይሌው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጣበት ዓመት ሻምፒዮን መሆን ችሏል።

1993 ዓ.ም ደግሞ ለመብራት ኃይል ልዩ የሚባል ዓመት ነበር። አንዋር ሲራጅ፣ አንዋር ያሲንን እንዲሁም ወንድማማቾቹን ስምኦን አባይና ዮርዳኖስ አባይ የያዘው የወቅቱ የመብራት ኃይል ስብስብም የሊጉን ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ ያነሳው በዚሁ ዓመት ነው። ዓመቱ ዮርዳኖስ አባይም 24 ግቦች ያስቆጠረበትና በባለፈው ዓመት የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ እስከተረከበው ድረስ 16 አመታት የዘለቀ የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት ከብር የተሰራበት ሲሆን፣ መብራት ኃይሎችም የሶስትዮሽ ድል የተቀዳጁበት ነው።
ሊጉ በተጀመረ በሶስት ዓመት እድሜው ሁለት ዋንጫ ማንሳት የቻሉት መብራት ኃይሎች፣ በ1994 ዓ.ም ሶስተኛ ድላቸውን እንደሚያስመዘግቡ ሰፊ ግምት ቢሰጣቸውም፤ አሳማኝ በሆነ መልኩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እጅ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ1995 የውድድር ዓመት ልዩ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ክለብን ሻምፒዮን ለማድረግ ጫፍ መድረስ መቻሉ ነው። የታሪኩ ባለቤት ለመሆን ከጫፍ የደረሰው ደግሞ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ሲሆን፣ ክለቡ ሊጉን ለማሸነፍ መጀመሪያው የክልል ክለብ ለመሆንም የቅዱስ ጊዮርጊሶችን የመጨረሻ ውጤትና ነጥብ መጣል ብቻ መጠበቅ በቂው ነበር።
ይሁንና ፈረሰኞቹ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በካሳዬ አራጌ ድንቅ የእግር ኳስ ፍልስፍና የሚመራውን ኢትዮጵያ ቡና በማሸነፍ ዋንጫውን ከአርባምንጭ አፍ ነጠቀዋል።ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መዋቅር መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ ሻምፒዮን በመሆንም ከአገሪቱ ክለቦች ግንባር ቀደም መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ክለብ የሊጉ ሻምፒዮን መሆን የቻለው በ1996 የውድድር ዓመት ነው። የታሪኩ ባለቤትም ሀዋሳ ከተማ ነው። ይህን ዓመት ልዩ የሚያደርገው ይህ ብቻ አይደለም። የሊጉ ሻምፒዮን የመሆን ፉክክሩ እስከ መጨረሻው ሳምንት መዝለቁም ጭምር ነው። በዚህ የውድድር ዓመት የሊጉ አሸናፊ ቀድሞ መለየት ባለመቻሉ፤ሀዋሳና አዲስ አበባ ላይ ሁለት ዋንጫዎች ማስቀመጥ ግድ ብሏል።
በከማል አህመዱ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የመጨረሻ ጨዋታቸውን ማሸነፍ ግድ ነበረባቸው። እናም የራሳቸውን እድል በራሳቸው ላይ መስረተው ወደ ሜዳ የገቡት ሀዋሳዎች፤ ከኒያላ ጋር ያደረጉትን የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በመርታት ዋንጫውን ከፍ አድርገዋል። ሻምፒዮን የመሆናቸው እጣ ፈንታ በሀዋሳ መሸነፍ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና እና ትራንስ ኢትዮጵያም ተጋጣሚዎቻቸውን ቢያሸንፉም በሀዋሳ ማሸነፍ ምክንያት ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ደግሞ ፈረሰኞቹን ከሻምፒዮንነት የሚያቆም ክለብ የጠፋባት ሲሆን፣ በአሰልጣኝ ሚቾ የሚመሩት ፈረሰኞችም ሊጉን ነግስውበታል።ፈረሰኞቹ የሊጉ ሻምፒዮንነት በ16 ክለቦች መካከልም የተካሄደው የ1999 የውድድር ዓመት በሃዋሳ ቢተካም፤ ከሚሊኒየሙ በኋላም ባሉት ቀጣዮቹ ሶስት ዓመታትም የሚያቆመው አልተገኘም። ፈረሰኞቹ በእነዚህ ዓመታት አሸናፊ ክለብ መሆናቸው አስደማሚ ብቃት በማሳየት ያስመሰከሩ ሲሆን፣ ደጋፊዎቻቸውን ጮቤ በማስረገጥም በድል አንቆጥቁጠውበታል።
የ2003 ዓ.ም ግን የፈረሰኞቹ አልነበረም። ይልቅስ ኢትዮጵያ ቡና ከ13 ዓመታት ጥበቃ በኋላ የመጀመሪያ የሊግ ሻምፒዮን የሆነበት ነው። ቡናዎች የመጨረሻ ጨዋታቸውን ሙገር ሲሚንቶን 2ለ0 በማሸነፍ ሻምፒዮን የሆኑበት ይህ ዓመትም በወቅቱ የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ያገኘ ሲሆን፣ ከ1996 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ መጨረሻው ሳምንት የዘለቀው የሻምፒዮንነት ፉክክር የታየበት ነው።
የ2004 ዓ.ም እንደሌሎች ዓመታት ሁሉ የሊግ ክብሩን ባጣ በቀጣዩ አመት ተጠናክሮ ብቅ የሚለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮን የሆነበት ነው።ይህ ዋንጫ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1990 በኋላ የተመዘገበ 10ኛ ድል ሆኗል፡፡ የፈረሰኞቹ የሊጉ የሻምፒዮንነት ጉዞ በ2005 በደደቢት ቢተካም፤2006ን ግን አላለፈም። ከዚህ በኋላ ያለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግም ፈረሰኞቹን ከማንገስ አልተቆጠበም።
ላለፉት ሰባት የውድድር ዓመታት ሻምፒዮኑን ለመገመት ቀላል ሆኖ በታየውና በፈረሰኞቹ የበላይነት በሚታወቀው የሊጉ ውድድር ዘንድሮ ግን ለየት ብሏል። በርከት ያሉ አስገራሚ ጉዳዮች የተከሰቱበት ሆኖም አልፏል፡፡ ዓመቱ በስፖርታዊ ጨዋነት በመጓደሉ ሊጉ ክብሩን ያጣባት፣ከተጫዋች እስከ አሰልጣኝ ቅጣቶች የተስተዋለበትም ነው። ቅጣቱም ከሜዳ እስከ ገንዘብ ብሎም እስከ እግድ የደረሰም ነበር።
በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ አልሆንልህ ብሎትም፤ ጨዋታዎችም እስከመጨረሻው ሳምንት በክረምት ወራት፣ በዶፍ ዝናብ፣ ጭቃና ውሃ ባዘለ ሜዳ እንዲካሄዱም አድርጓል። በተለይ ሁሉም የአዲስ አበባ ክለቦች የሚጫወቱበት የአዲስ አበባ ስታዲየምና አንዳንድ የክልል ሜዳዎች ጨዋታዎችን ማስተናገድ ታክቷቸው ተስተውሏል። መርሐ ግብር ለማሟላት በሚል ብቻ ተጫዋቾች ሜዳ ገብተው ሲንቦራጨቁም ተስተውሏል። ይባስ ብሎም ጨዋታዎቹ ተቋርጠዋል፤ተራዝመዋልም።
በመሰል ሁነቶችና ክስተቶች የታጀበው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሌላ አዲስ መገለጫም ነበረው። በ1995 ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤በ1996 ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ከሰባት ዓመት በፊት በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና ሻምፒዮን ሲሆኑ፤ ሊጉ እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ የዋንጫውን ባለቤት እንዳላሳወቀው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፐሪሚየር ሊግም ይህ ታሪክ ተደግሟል።
ፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን እስከመጨረሻዎቹ ሶስትና አራት ሳምንታት መርሐ ግብሮች ድረስ በርካታ ክለቦች ሰፊ ዕድል ይዘው አጓጊ ፉክክር ሲያደርጉ ቢቆዩም በሂደት የዋንጫው ተፎካካሪ ክለቦች ቁጥር እየመነመነ መጥቶ በመጨረሻ የሁለት ክለቦች ብቻ ፍጥጫ ሆኗል። ከሳምንት ሳምንት መሪነቱን እየተነጣጠቁ በቅርብ ርቀት የሚከተሏቸውን ቡድኖች በነጥብ እየራቁ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ድረስ የዘለቁት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባ ጅፋር ሆነዋል።
በዚህም ሻምፒዮኖቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ51 ነጥብና በ19 ንፁህ ጎል ሊጉን በቀዳሚነት ሲመሩ፣ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለው ጅማ አባ ጅፋር እርስ በርስ ሲገናኙ በሚለው ተበልጦ 51 ነጥብና በ19 ጎል ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል። ይህ ውጤትም ከ14 ዓመታት በኋላ የሊጉ ሻምፒዮን በመጨረሻው ጨዋታ ውጤት እንዲወሰን ያስገደደው ሲሆን፣ ዋንጫውም ጅማና አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ ባለቤቱን እንዲጠብቅ አስገድዶታል።
ለዚህ መልስ በመስጠት የዋንጫውን ማረፊያ በሚወስነው የሰላሳኛው ሳምንት የሊጉ የመጨረሻ ፍልሚያም ትናንት ጅማ ላይ አባጅፋር ከአዳማ ከተማ፤ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሃዋሳ ከተማን አገናኝቷል። በተመሳሳይ ሰዓት የተካሄደው ጨዋታ ታዲያ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ ሻምፒዮንን አስተዋውቋል። መድረሻውን ጊቤ ማዶ አድርጎ 306 ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ በአባጅፋር አገር ጅማ አድርጓል።
በጅማ ስታዲየም የተደረገውን ጨዋታ አባጅፋሮች ኦኪኪ አፉላቢ በ9፣ በ58፣ በ66 እና 82ኛው ደቀቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው አራት ግቦች እና ተመስገን ገብረ ኪዳን 32ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት አንድ ግብ በአጠቃላይ አምስት ለዜሮ ጨዋታውን አሽንፈዋል።
የጅማ ዞንን ይወክል የነበረው ጅማ አባቡና በወረደበት ዓመት፤ትልቁን ሊግ የተቀላቀለው የጅማ ከተማ ክለብ «ጅማ አባጅፋር» ሊጉን በተቀላቀለ የመጀመሪያ ዓመት ድንቅ አቋምን አሳይተዋል። የአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ እንዳስመለከተን ከከፍተኛ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያልፉ ክለቦች በመጀመሪያ ተሳትፏቸው ላለመውረድ እንጂ ለሻምፒዮንነት ሲፋለሙ አይስተዋልምና ይህን ታሪክ የቀየሩት የአባ ጅፋሮቹ ልጆች የብዙዎችን አድናቆት እንዲቸራቸው አስገድዷል።ይህን ታሪክ የመቀየርና የመስራት አደራም ከክለቡ ተጫዋቾቹና ደጋፊዎች በተጓዳኝ በዋናነት በአንጋፋው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ፊት አውራሪነት እውን ሆኗል። ጅማ አባ ጅፋሮች የመጀመሪያ ተሳትፎ የመጀመሪያ የሊግ ድልም በታሪክ ከአዋሳ ቀጥሎ ሁለተኛው የክልል ክለብ ያደርጋቸዋል።
ፈረሰኞቹ የክረምቱን መግባት ተከትሎ ለጨዋታ በማያመቸው አዲስ አበባ ስታዲየም ያደረጉትን ጨዋታ፤ሜዳው ኳስን እንደ ልብ እንዳይጫወቱ ሲያደርጋቸውም ተስተውሏል።እጅግ ማራኪ ድባብ በዝናብ ታጅቦ የተካሄደውን ጨዋታ፣ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ባገኙት የፍፁም ቅጣት ምት ሳላዲን በርጌቾ፣ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሙሉአለም መስፍን ባስቆጠራት ግብ ጨዋታውን ማሸነፍ ቢችሉም በአጠቃላይ ውጤት በግብ ክፍያ ተበልጠው የለመዱትን ዋንጫ መሪር በሆነ መልኩ ለአባ ጅፋሮች አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል። ውጤቱን ተከትሎ ጅማ ላይ ፌሽታና ፈንጠዝያው ሲደራ፣ አዲስ አበባ ስታዲየም ሃዘንና ቁጭት ነግሶ ታይቷል።
በአጠቃላይ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አባጅፋሮችን ሲያንግስ ጊዮርጊሶችን አስከትሏል። ኢትዮጵያ ቡና ሶስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤መቀሌ ከተማና አዳማ ከተማ አራተኛና አምስተኛ ሆነዋል። ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ከመጀመሪያው እስካሁን በመዝለቅ ከሚታወቁ ውጤታማ ተብለው ከሚጠቀሱ የአገሪቱ ክለቦች አንዱ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ውጤት ርቆት ወደ ብሔራዊ ሊግ ላለመውረድ ሲታገል የተመለከትነው አንጋፋው ኢትዮ ኤሌክትሪክ፤ ከዓመታት በኋላ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጉን በይፋ ተሰንብቷል።እንደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አርባ ምንጭ ከተማና ወልድያ ከተማ ሊጉን የተሰናበቱ ክለቦች ሆነዋል።
የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ናይጄሪያዎቹ ኦኪኪ አፉላቢና በሃያ ግብ አሸናፊ ሆኗል። በአጠቃላይ ከአሳፋሪ መገለጫዎቹ ባሻገር የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ መጨረሻው ሳምንት የታየው የአንገት ለአንገት ትንቅንቅ ብዙዎችን አስድስቷል።

(አዲስ ዘመን)